Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“የአንድነት ቀን“ በመከላከያ ሠራዊት እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው “የአንድነት ቀን“ በመከላከያ ሠራዊት እየተከበረ ነው

“ስናብር ስናምር” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ የሚገኘው የአንድነት ቀን የአንድነትና የህብረት መገለጫ በሆነው በመከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

በዝግጅቱ የተለያዩ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎሉ የኪነጥበብ ዝግጅቶች በመከላከያ የሙዚቃ ቡድን ታጅበው እየቀረቡ መሆኑን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዝግጅቱ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሀም በላይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች እና የሰራዊት አባላትና ቤተሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ በብዝሃነት ውስጥ ያለ አንድነቷን ስታጠናክር ውበቱ ጥልቅና የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

“አንድነት ኢትዮጵያ የቆመችበት አለት ነው” ሲሉም የኢትዮጵያውያንን የአንድነት ኃይል በአፅንኦት አንስተዋል።

የጠንካራ ሀገር የውጭ ግንኙነት መሰረቱ ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያውያንም ውስጣዊ አንድነታቸውን ማጠንከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

“አንድነት ውርሳችን፣ ምግባራችን፣ የመጪው ዘመን ህልማችን እውን መሆን ማረጋገጫ ቁልፍ መሳሪያችን ነው” ብለዋል።

መንግስት የሀገር ክብርና አንድነትን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ መምራትና ማስተባበርን እውን እያደረገ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው የአንድነት ምሳሌ ከሀገር መከላከያ በላይ የሚገልጽበት ቦታ የለም ነው ያሉት።

ባለፉት አራት ዓመታት መከላከያ ሠራዊት ከፓርቲ መሳሪያነት ወጥቶ የሀገርና ህዝብ መከታ ሆኖ እንዲገነባ መደረጉንም ተናግረዋል።

 

Exit mobile version