አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተማችንንና የዙርያዋን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሰላማዊ እና የተረጋጋ የማድረግ የጋራ እንቅስቃሴ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።
ከንቲባዋ ይህን በማድረግ የጠላትን ከንቱ ምኞት ማክሸፋችንን ልንቀጥል ይግባል ብለዋል።
ነዋሪዎች፣ የመንግስት መዋቅር፣ በየአካካቢው የተደራጁ የህዝባዊ ሰራዊት አባላት፣ የአዲስ አበባ፣ የፌደራልና የኦሮምያ ልዩ ዞን የፀጥታ አካላት፣ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዘመን መለወጫ በዓል ከዋዜማው አንስቶ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በከተማዋ በዓሉን አስታኮ የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈፀም የከተማዋን ሰላም ለማወክ፣ የገበያ አቅርቦት እጥረት እንዲያጋጥምና ይህን ተከትሎም ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ንረትን በማስከተል ህብረተሰቡን ውጥረት ውስጥ ለመክተት አቅደው ሲዘጋጁና ሲያስተባብሩ የነበሩ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም በሁሉም አካላት የጋራ እንቅስቃሴ በመክሸፉ በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ ማለፍ ችሏል ያሉት ከንቲባዋ፥ “ከዚህ የምንማረው አንድነታችን መተባበራችን የአሸናፊነታችን ሚስጥር መሆኑን ነው” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡
አሁንም፥ ቀጣዮቹንም ጊዜያት በተለይም የተለያዩ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን አከባበር ጨምሮ የተጀመረው ከተማዋና የዙርያዋን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሰላማዊ እና የተረጋጋ የማድረግ የጋራ እንቅስቃሴ ስራችንን አጠናክረን በመቀጠል የጠላትን ከንቱ ምኞት ማክሸፋችንን እንቀጥል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

