አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የሚኒስትሮች የጋራ ግብረሃይል ጊዜያዊ የመጀመሪያ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
ግብረ ሃይሉ ባለፉት 8 ወራት ማለትም ከመስከረም እስከ መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም የተፈፀሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ነው በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገው ።
ለምርመራው 11 የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ 158 ባለሙያዎች ሙያዊ ስልጠና ወስደው የምርመራ ስራው መከናወኑ ተጠቁሟል፡፡
በትግራይ ክልል የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ክልሉ አሁንም በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር በመሆኑ ግብረሃይሉ አብዛኛው ምርመራ በአማራና አፋር ክልል ላይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡
በአማራና አፋር ክልሎች በተከናወነው ምርመራም 2 ሺህ 831 ሰዎች በአሸባሪው ህወሓት መገለዳቸውን እና 452 ሰዎች ላይ ከፍተኛ ኢ- ሰብዓዊ የመብት ጥሰት መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም 36 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ፣ 26 ሺህ 334 ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ከ865 ሺህ ኩንታል በላይ እህል መውደሙ፣ 411 ሺህ የቁም እንስሳት መገደላቸው እና ከ2 ሺህ 500 በላይ የጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች መውደማቸውን የመጀመሪያው ሪፖርቱ ግኝት አመላክቷል፡፡
175 ወረዳዎችን ለማካለል ተሞክሮ በተሰራው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ስራ በአማራ ክልል 9 ሺህ 552 የምስክሮች ቃል በአፋር ክልል 517 የምስክሮች ቃል የተሰማ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በሁለቱም ክልሎች 3 ሺህ 387 የሰነድ ማስረጃ 2 ሺህ 599 የፎቶና የተንቀሳቃሽ ምስል ሰነዶችም ቀርበው ምርመራ ተደርጓል ተብሏል፡፡
ከፍርድ ውጪ ግድያ ከተፈጸመባቸው 2 ሺህ 831 ንጹሃን ዜጎች አብዛኛዉ በሽብር ቡድኑ ህወሓት በሰሜን ሸዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ ደግሞ የሽብር ቡድኑ ሸኔ በእቅድ ተመስርተው ግድያውን መፈፀማቸውን መረጋገጡ ተጠቅሷል፡፡
የግድያ ሁኔታዎቹ በተኩስ እሩምታ ፣ በጩቤ እና የሰውነት ክፍልን ቀድሞ እየቆራረጡ ነው ያለው የምርመራ ግኝቱ አራት የጅምላ መቃብሮችም በጋሊኮማ ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን አንፆኪያ እና ጪና መገኘታቸውን ተመላክቷል ።
በጸጋዬ ወንደሰን

