ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጊዜያዊ የመጀመሪያ ሪፖርት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የሚኒስትሮች የጋራ ግብረሃይል ጊዜያዊ የመጀመሪያ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
ግብረ ሃይሉ ባለፉት 8 ወራት ማለትም ከመስከረም እስከ መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም የተፈፀሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ነው በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገው ።
ለምርመራው 11 የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ 158 ባለሙያዎች ሙያዊ ስልጠና ወስደው የምርመራ ስራው መከናወኑ ተጠቁሟል፡፡
በትግራይ ክልል የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ክልሉ አሁንም በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር በመሆኑ ግብረሃይሉ አብዛኛው ምርመራ በአማራና አፋር ክልል ላይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡
በአማራና አፋር ክልሎች በተከናወነው ምርመራም 2 ሺህ 831 ሰዎች በአሸባሪው ህወሓት መገለዳቸውን እና 452 ሰዎች ላይ ከፍተኛ ኢ- ሰብዓዊ የመብት ጥሰት መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም 36 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ፣ 26 ሺህ 334 ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ከ865 ሺህ ኩንታል በላይ እህል መውደሙ፣ 411 ሺህ የቁም እንስሳት መገደላቸው እና ከ2 ሺህ 500 በላይ የጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች መውደማቸውን የመጀመሪያው ሪፖርቱ ግኝት አመላክቷል፡፡
በጸጋዬ ወንደሰን