አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን መክፈቻ ስነ-ስርዓት መካሄድ ጀምሯል፡፡
ሁለቱ ምክር ቤቶች ባለፈው 2014 ዓ.ም የ1ኛ ዓመት የስራ ዘመናቸውን አጠናቀው በ2015 ዓ.ም የ2ኛ ዓመት የስራ ዘመናቸውን የሚይዙ ይሆናል፡፡
በዚህም 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡
በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንቷ የመንግስት ዕቅድን በሚመለከት ለሁለቱ ምክር ቤቶች ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመርሐ ግብሩ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

