Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ  በደባርቅ ከተማና በዳባት ወረዳ 39 ሚሊየን ብር መድቦ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የምዕራብ አማራ ቤቴ ፕሮጀክት በደባርቅ ከተማ አስተዳደርና በዳባት ወረዳ  39 ሚሊየን ብር መድቦ  ለተፈናቃዮች ፣ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖችና ለተቋማት ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።

 

ፕሮግራሙ  ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በአካባቢው ለሚገኙ ወገኖችና ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ፣ የዕለት ደራሽ ምግብና የገንዘብ ድጋፍ  አድርጓል ነው የተባለው፡፡

 

ከ 1ሺህ 100 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግና መምህር በመቅጠር የተፋጠነ ስርዓተ ትምህርት በመዘርጋት እያስተማረ መሆኑ ተጠቅሷል።

 

በወርልድ ቪዥን ኢትዮጰያ ምዕራብ አማራ ቤቴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሮ እየሩሳሌም እያዩ እንዳሉት÷ በሁለቱ አካባቢዎች ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት  ወንበሮች ፣ ድንኳኖች እና የቤት ውስጥና ውጭ የልጆች መጫዎቻዎች ድጋፍ ተደርጓል።

 

በቀጣይም  በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ህጻናትና ታዳጊዎች ወደ ትምህርታቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናረዋል፡፡

 

የዳባት ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አትርሳው ክንዴ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ በወረዳው ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት ካደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር በችግር ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች በነፍስ ወከፍ 4ሺህ ብር በመስጠት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አስችሏል ብለዋል ።

 

የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት መመምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ የሽወርቅ  ሞላ በበኩላቸው÷ ፕሮግራሙ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና በስርዓተ ጾታ ላይም የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት እየሠራ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

 

በበላይነህ ዘለዓለም

Exit mobile version