ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በደባርቅ ከተማና በዳባት ወረዳ 39 ሚሊየን ብር መድቦ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የምዕራብ አማራ ቤቴ ፕሮጀክት በደባርቅ ከተማ አስተዳደርና በዳባት ወረዳ 39 ሚሊየን ብር መድቦ ለተፈናቃዮች ፣ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖችና ለተቋማት ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።
ፕሮግራሙ ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በአካባቢው ለሚገኙ ወገኖችና ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ፣ የዕለት ደራሽ ምግብና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ነው የተባለው፡፡
ከ 1ሺህ 100 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግና መምህር በመቅጠር የተፋጠነ ስርዓተ ትምህርት በመዘርጋት እያስተማረ መሆኑ ተጠቅሷል።
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጰያ ምዕራብ አማራ ቤቴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሮ እየሩሳሌም እያዩ እንዳሉት÷ በሁለቱ አካባቢዎች ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት ወንበሮች ፣ ድንኳኖች እና የቤት ውስጥና ውጭ የልጆች መጫዎቻዎች ድጋፍ ተደርጓል።
በቀጣይም በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ህጻናትና ታዳጊዎች ወደ ትምህርታቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናረዋል፡፡
የዳባት ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አትርሳው ክንዴ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ በወረዳው ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት ካደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር በችግር ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች በነፍስ ወከፍ 4ሺህ ብር በመስጠት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አስችሏል ብለዋል ።
የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት መመምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ የሽወርቅ ሞላ በበኩላቸው÷ ፕሮግራሙ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና በስርዓተ ጾታ ላይም የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት እየሠራ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በበላይነህ ዘለዓለም