Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ድንበሮቿን ለሰዎች ዝውውር ዝግ አደረገች

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሉም የሃገሪቱ ድንበሮች ለሰዎች ዝውውር ዝግ መደረጋቸውን ተናገሩ።

የድንበር መዘጋቱ የሎጅስቲክስ አቅርቦት ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት እንደማያካትት አስታውቀዋል።

በዛሬው እለት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የተገመገሙ ሲሆን፥ ማህበረሰቡ ከንክኪ ተራርቆ እንዲንቀሳቀስ የተላለፈው መልዕክት ባለፉት ቀናት በአግባቡ እየተፈጸመ አይደለም ተብሏል።

ቅዳሜ እና እሁድ በነበረው የእምነት ተቋማት መርሃ ግብሮች ላይም በቂ የመከላከል እርምጃ እንዳልተወሰደ ተገምግሟል።

የሃይማኖት አባቶች በቀጣይ ምዕመኖቻቸውን ከማስተማር ባለፈ በተግባር እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተላልፏል።

ሰዎችን በአንድ ቦታ የሚያሰባስቡ መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛዎች እንዲሁም ጫት ቤቶች ላይ በቀጣይ ጠንካራ እርምጃ የፀጥታ ሃይሉ እንዲወስድም አቅጣጫ ተቀምጧል።

ከስብሰባ ጋር ተያይዞም የመንግስት ተቋማት እንዳይሰበሰቡ እገዳ ባይጣልም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ተላልፏል።

በተጨማሪም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሰዎችን ንክኪ ለመቀነስ እንደየመስሪያ ቤቶቹ ሁኔታ እየታየ ከፊል ሰራተኞች ከቤታቸው ሆነው ስራቸውን የሚሰሩበት መንገድ እንዲመቻችም መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ቫይረሱ በኢትዮጵያ በ11 ሰዎች ላይ የተገኘ ቢሆንም በቀጣዮቹ ቀናት በመቶዎች ሊያድግ ስለሚችል ሁሉም ሰው ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ተመድቦ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ሃብት የማሰባሰብ ስራው ይቀጥላልም ነው ያሉት።

የዓለም ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለመታደግ በፍጥነት 100 ቢሊየን ዶላር መመደብ ካልቻሉ የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ይገባልም ብለዋል።

ለዚህም የቡድን 20 አባል ሃገራትን ጨምሮ ከሌሎች ለጋሽ ሃገራትና ተቋማት ጋር በመሪዎች ደረጃ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም አውስተዋል።

የኮሮና ቫይረስን በኢትዮጵያ መከሰት ተከትሎ በሸቀጦች ላይ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version