Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“አርቲስት ዓሊ ቢራ የሀገር ፍቅር ምልክት ነው”- አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለገቡ የጥበብ ሰው አርቲስት ዓሊ ቢራ “የሀገር ፍቅር ምልክት ነው” ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡

አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በአዲስ አበባ ከተማ የወዳጅነት ዐደባባይ በተካሔደው የአርቲስት ዓሊ ቢራ የአስከሬን ሽኝት ሥነ ስርዓት ላይ÷ በአርቲስት ዓሊ ቢራ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን በኢፌዴሪ መንግሥት እና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስም ገልጸዋል፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግርም÷ አርቲስት ዓሊ ቢራ ብዝኃነትን ከአንድነት አጣምሮ የያዘ የተሟላ የኪነ ጥበብ ሰው ነበር ብለዋል፡፡

ዓሊ ቢራ ልሣን እንደነበር ጠቅሰው÷ በሚናገራቸው እና በዘፈነባቸው ቋንቋዎች ሁሉ አንድነትን አቀንቅኖባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በይዘት ረገድም ዓሊ ያላነሳው ጉዳይ የለም ያሉት አፈ ጉባዔው÷ ስለፍቅርና ነጻነት፤ ስለእኩልነትና ፍትሕ ደጋግሞ መዝፈኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሁሉም እንደሆኑ እና ሁሉንም እንዳገለገሉ መሔድ መታደል እንደሆነ ጠቁመው÷ ይህን ዕድል የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው፤ አንዱም አርቲስት ዓሊ ቢራ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተነካች እና በከፋት ጊዜ አርቲስተ ዓሊ ቢራ የመጀመሪያ ተሰላፊ እንደነበር ያስታወሱት አፈ ጉባዔ አገኘሁ÷ አርቲስት ዓሊ ቢራ “የሀገር ፍቅር ምልክት ነው” ሲሉ በአጽኦት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናው የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ አንጋፋ ከሚባሉ ስመ ጥር አርቲስቶች አንዱ አርቲስት ዓሊ ቢራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ለባለቤቱ፣ ለቤተሰቦቹ ፣ ወዳጆቹ እና ለአድናቂዎቹ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version