አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የማዕድን ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት ለዓለም አቀፍ ታዳሚያን ለማስተዋወቅ ያግዛል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡
ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት ለማስተዋወቅ በርካታ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናልም ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ “Mintex” ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ፣ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል፡፡
በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ እንዳሉት÷ ኤክስፖው መዘጋጀቱ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ታዳሚያን ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት በግላጭ እንዲያዩ ያግዛል።
ዘርፉ ለህገወጥ ተግባር ተጋላጭ ስለሆነም መከላከሉ ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይኖርብናልም ብለዋል::
“ማዕድን በባህሪው አላቂ በመሆኑም የአካባቢ ደህንነትና ጥበቃን በማስቀደም ከሰራን ዘርፉ ህዝባችንን ከድህነት ለማስወጣት ያስችላልም” ነው ያሉት::
የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከማዕድን የምታገኘው 1 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው ብለዋል::
ይህን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም በሚቀጥሉት 10 እና 15 አመታት ወደ 17 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኤክስፖው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሕዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በዘቢብ ተክላይ

