Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2050 የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን ዜሮ ለማድረስ የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥታ እየሠራች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2050 የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን ዜሮ ለማድረስ ከፓሪሱ ስምምነት ጋር የሚጣጣም የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥታ ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በግብጽ ሻርም ኤል ሼክ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ነው።
 
በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት 25 ቢሊየን ችግኞች መትከሏን ገልጸዋል፤ ይህም አንድ ዜጋ 250 ችግኞች መትከሉን በመጥቀስ።
 
በንግግራቸውም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ ድርቅ እና ጎርፍ አደጋ መጠቃቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያም ስጋት ላይ መሆኗን አውስተዋል።
 
መጥፎ አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚዎች መቀየር ችለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የህዝቡን አደጋ የመቋቋም አቅም ማሳደግ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን ደህንነት መጠበቅ መቻሉንም አስረድተዋል።
 
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ዘላቂ፣ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ እና ርካሽ ታዳሽ ሀይልን ለዜጎቿና ለቀጠናው ለማዳረስ እየሰራች መሆኑንም አንስተዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ወደ አረንጓዴ ልማት ለመሸጋገር፥ በደን ማልበስ፣ በደን መልሶ ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል በኩል ፈጣን ለውጥ ማሳየቷን ጠቅሰዋል።
 
አያይዘውም የ10 አመቱ የእድገት እና ልማት እቅድም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አስረድተዋል።
 
የአረንጓዴ አሻራ ስራ ብሔራዊ አረንጓዴ ባሕል እንዲስፋፋ በማድረግ የተለያዩ ትሩፋቶችን ማስገኘት መቻሉንም አንስተዋል፡፡
 
በተጨማሪም ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በማጋራት በቀጠናው የድንበር ተሻጋሪ ሥነ ምህዳራዊ አስተዳደር ትብብር እንዲጠናከር አድርጓል ነው ያሉት፡፡
 
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ የኃይል ሽግግር ላይ ያላትን ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል አቅም ለመጠቀም መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትም አስረድተዋል፡፡
 
ከዓለም ህዝብ 17 በመቶ የሚሆነውን የምትይዘው አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ አህጉር መሆኗን ጠቁመው ÷ በበካይ ጋዞች ልቀት ረገድም አፍሪካ 5 በመቶ የሚሆነውን እንደምታበረክት አንስተዋል፡፡
 
የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ትብብር እና በቂ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ ይሁን እንጅ አፍሪካ ከዓለም የአየር ንብረት ፈንድ ከ5 በመቶ በታች የምታገኘው በዋናነት በብድር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ግቦችን ማሳካትቢቻልም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አሁንም የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ እተፈተነች በመሆኑ ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ችግሩ 100 ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎችን ድህነት ውስጥ ሊከት እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ መንግስት የተደረገው የሀገር ወስጥ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ምቹ የአየር ንብረት ሁኔታን ለመፍጠር አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
 
ይሁን እንጂ እየተሰፋፉ ካሉት ተግዳሮቶች አንጻር ተጨማሪ ፈንድ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡
 
በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ለአፍሪካ የተጨመረው የገንዘብ ድጋፍ አህጉሪቱ በዘርፉ ካጋጠማት ችግር ጋር የሚጣጣም መሆን እንደለበትም ጠቁመዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው የሚገኙ አረንጓዴ አሻራ፣ አረንጓዴ ኢነርጂ፣ የሌማት ትሩፋት እና የመሳሰሉት አየር ንብረትን መሰረት ያደረጉ ፖሊሲዎቿ የአፍሪካ ሀገራትን የሚያነሳሱ እና ቀጣናዊ ዲፕሎማሲን የሚያበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡
Exit mobile version