አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ዝርዝር ዕቅድ ላይ በኬንያ ናይሮቢ ለቀናት ሲወያይ የቆየው የኢፌዴሪ ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
ልዑኩ አዲስ አበባ ሲገባ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዚህ ወቅት፥ “ባለፉት ጊዜያት ለሰላም ስንጥር ነበር፤ የሰላም ውይይቱም ጥሩ አጋጣሚ ነው” ብለዋል።
አያይዘውም፥ “በናይሮቢ፥ በፕሪቶሪያ የተደረሠው የሠላም ስምምነት በእኛ በኩል ወደ ተግባር በሚገባበት ላይ ተወያይተናል” ብለዋል።
“ለሰላም እና ለህዝቡ ስንል የተፈራረምንበትን እንፈፅማለን፤ ለተግባራዊነቱም እንታገላለን” ነውም ያሉት።
በሰላም ስምምነቱ መሠረት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ማሣለጥ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመርና የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበት ዝርዝር ዕቅድ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አዛዥና የሕወሓት ታጣቂዎች አዛዥ በናይሮቢ ሲያደርጉት የነበረውን ውይይት በስምምነት ፊርማ ማጠናቀቃቸው ይታወቃል።
በቅድስት ተስፋዬ

