Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትና ተደራሽነት ላይ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትና ተደራሽነት ጉዳይ ላይ በመምክር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

ኮሚቴ ው በስብሰባው በሀገሪቱ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገምግሟል፡፡

በድርቅ፣ በጎርፍ እና በግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት እንደሚፈልግና የሁሉንም ዜጋ ርብርብ እንደሚሻም ተጠቁሟል፡፡

በትግራይ፣ አፋር፣ አማራና በሌሎች አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች መንግስት አስቾኳይ የሰብዓዊ እርዳታ በማድረስ ላይ መሆኑንም ኮሚቴው አንስቷል፡፡

ለችግር የተጋለጡ ተረጂዎችን በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚያስፈልግ የኮሚቴው ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳስበዋል፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ለችግር ከተጋለጡት ዜጎች ጎን ለጎን ባለፉት ዓመታት በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ተረጂዎችም ትኩረት እንደሚሹም ተናግረዋል፡፡

በግጭት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው የቆዩ ተማሪዎችና በተለያየ ምክንያት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችም ከሰብዓዊ ዕርዳታ በተጨማሪ የሥነ-ልቦና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አቶ ደመቀ ጠቁመዋል፡፡

የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ሀገሪቱ ካላት የተረጂዎች ቁጥር አንፃር መንግስት ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አቶ ደመቀ÷ ሁሉም ሴክተሮች ሐብት ማሰባሰብና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ለመድረስ መቀናጀት አለባቸው ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የልማት አጋሮችም ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለማገዝ ባላቸው አቅም ሁሉ መረባረብ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የግብርናና የከተማ ሴፍትኔት መርሐ ግብሮች የተረጂዎችን ሕይወት በዘላቂነት ለመቀየር በሚያስችል መልኩ ሊሰራባቸው እንደሚገባም ነው ያነሱት።

የሚመለከታቸው ሴክተሮች፣ የፌዴራልና የክልሎች የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ተቋማት ልምዳቸውንና ሐብታቸውን በማቀናጀት በዕለት ተዕለት እቅዳቸዉ ውስጥ በማካተት መረባረብ እንዳለባቸ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈም ዜጎች በዘላቂነት ከተረጂነት በሚላቀቁበት መንገድ ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸው በአስቸኳይ ስብሰባው ላይ አቅጣጫ መሠጠቱን የብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ መረጃ አመላክቷል፡፡

ብሔራዊ ኮሚቴውም በየሳምንቱ በመገናኘት የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት፣ አቅርቦትና ተደራሽነት ሁኔታ እየገመገመ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

Exit mobile version