አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀዋሳ እና አዳማ ከተማ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የፀረ ተዋህስ መድሃኒት ርጭት ስራ በዛሬው እለት ተከናውኗል።
በሀዋሳ ከተማ የፀረ ተዋህስ መድሃኒት ርጭት ስራው ከማለዳው 12:00 ሰዓት እስከ 4:00 ሰዓት ድረስ የተካሄደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።
የከተማዋ ጎዳናዎች ከማንኛውም ተሽከርካሪዎች ነፃ በማድረግ የፀረ ተዋህስ መድሃኒት ርጭት ስራው መከናወኑን ነው የተገለፀው።
በተመሳሳይ በአዳማ ከተማ የፀረ ተዋህስ መድሃኒት ርጭት ስራው በተለይም የህብረተሰቡ እንቅስቃሴ በሚበዛቸው አካባቢዎች ላይ በዛሬው ዕለት በስፋት መካሄዱን የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
የመድሃኒት ርጭቱ በሽታ አስተላላፊ ተህዋሲያንን ለማጥፋት ያለመ ሲሆን፥ በተለይም በኮሮናቫይሰር ተበክለዋል ተብሎ የተጠረጠሩ አካባቢዎችን የሚያፀዳ ነው ብሏል የከተማ አስተዳደሩ።
የከተማዋ ነዋሪዎችን ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን በመቆጠብ እና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም የከተማ አስተዳደሩ መልዕክት አስተላልፏል።
በአዲስ አበባ ከተማም ባሳለፍነው እሁድ በከተማዋ በሚገኙ 13 ዋና ዋና መንገዶች ላይ የፀረ ተዋህስ መድሃኒት ርጭት ስራ መከናወኑ ይታወሳል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

