አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን መገናኛ ብዙኃን በሚያከናውኗቸው የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራዎች ላይ በማንኛውም አካል የሚፈጸም ማዋከብ እንዲቆም አሳሰበ።
ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ የፍትሕ አካላት የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራን ሊያግዙ እንጂ ሊያደናቅፉ እንደማይገባ አስገንዝቧል።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 2፤ 3/ለ እና 4 እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 48 መሠረት መገናኛ ብዙኃን የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው” ጠቅሷል።
ለዴሞክራሲያዊ እና ተጠያቂነት ለሰፈነበት ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን የማግኘትና የመመርመር የአሠራር ነጻነት አልፎ ተርፎም የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው መደንገጉንም አስታውሷል።
የምርመራ ጋዜጠኝነትን ከማበረታታት አንፃርም ከሕጋዊ ማሕቀፎች ባለፈ እንደ መንግሥት አቅጣጫ ተይዞ እንዲሠራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማሳሰባቸውንም ነው ያነሳው።
በመርሕ ደረጃ የዜጎች መብት የተረጋገጠበት የዴሞክራሲ ባህል የሚጎለብትበት እና ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ሥርዓት ለመገንባት የፍትሕ አካላት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራት እጅግ ጠቃሚ መሆኑንም አንስቷል።
ይህ ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ያለምንም መታወክና እንቅፋት ብቁ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ መሥራት እንዲችሉ መረጃ የማግኘት፣ የመሰብሰብ፣ የመመርመር እና የማሠራጨት መብታቸው ከማንም በላይ በፍትሕ አካላት ሲረጋገጥ እና ጥበቃ ሲደረግለት መሆኑንም አስታውሷል።
ከዚህ በተቃረነ አግባብ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ ላይ በማንኛውም መንገድ እክል መፍጠር፣ የዜጎችን መብት መደፍጠጥ፥ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠር እንዲሁም ተጠያቂነት እንዳይሰፍን ከአጥፊዎች ጋር እንደመተባበር ይቆጠራልም ነው ያለው።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራዎች እንዲቆሙ ትዕዛዝ የመስጠት አዝማሚያ እየስተዋለ መምጣቱንም ጠቁሟል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙኃን ሥራ አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት ከመወጣት አንፃር መገናኛ ብዙኃን በሚያከናውኗቸው የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራዎች ላይ በማንኛውም አካል የሚፈጸም ማዋከብ እንዲቆምም አሳስቧል።
በተለይም የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ አጋዥና ተዋናይ መሆን የሚጠበቅባቸው የፍትሕ አካላት ለዚህ ሥራ አጋዥ እንጂ እክል እንዳይሆኑም ጥሪውን አቅርቧል።

