አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብዝሃ ቋንቋና ሃይማኖት ባለቤት በሆነችው አዲስ አበባ የአደባባይ በዓል የሆነውን የጥምቀት በዓል በአብሮነት፣እሴቱንና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ማክበር ይገባል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር ሰላምን በመጠበቅና ልማትን በጋራ ሲሰሩ የነበሩት በጉለሌ ክ/ከተማ እና በአጎራባች የሸገር ከተማ አስተዳደር አካኩ መነ አቢቹ የሱሉልታና የቡራዩ ክ/ከተማ የመንግስት አመራሮች፣ የተለያዩ የእምነት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች እና ነዋሪዎች በተገኙት ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ በአብሮነት የደመቀ የብዝሃ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ባለቤት የሆነችው ከተማችን የአደባባይ በዓል የሆነውን የጥምቀት በዓል በአብሮነት እሴቱንና ባህላዊ ትውፈቱን ጠብቆ ማክበር ይገባል ብለዋል።
አዲስ አበባ ውስጥ ለመመሸግ የሚፈልገውን የፀረ ሠላም ሃይል ነዋሪው ክፍተት ስለማይሰጠው አላማውን ማሳካት አልቻለም ያሉት ከንቲባዋ÷ልክ እንደ ትላንቱ ለሰላማችን በጋራ እንቁም ሲሉም አሳስበዋል።
የጉለሌ ክ/ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ኦሜጋ ÷ በዓሉን በሰላምና በድምቀት ለማክበር ጉለሌ ክ / ከተማ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የጉለሌ ክ/ከተማ እና የሸገር ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ለሰላማችን ዘብ እኛው ነን፤ የጥምቀት በዓልን በሰላም እንዳይከበር የተለያዩ የጥፋት ሴራ ለሚደግሱትም እድሉን አንሰጣቸውም ብለዋል።
ወጥቶ ለመግባት ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ÷ በመተባበርና መደጋገፍ ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን ሠላምና ልማት አንድ ሆነን እንስራለን ሲሉ ገልጸዋል።
የአንድነታችን ሚስጥር በውይይት ችግሮቻችን መፍታት መቻላችን ነው፤ ወጣቶችም የአባቶች ምክር ተቀብለን ለስላማችን ከፀጥታ አካላት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሰራለን ብለዋል።
የልማት ሥራዎች ፥ ሥራ እድል ፈጠራ፣ ሰላምንና ፀጥታን የተመለከቱ ጉዳዮች ከተሳታፊዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡