Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ስለሚገኝበት ሁኔታ አምባሳደር ምስጋኑ ገለጻ አድርገዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት የኢትዮጵያን አቋም ለሊቀመንበሩ ያስረዱ ሲሆን÷ የሶስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስራ መከናወኑ መቀጠል እንዳለበት ኢትዮጵያ የፀና አቋም እንዳላት ገልፀዋል።

ግብፅ የአባይን ውሃ እና ግድቡን የፖለቲካ መልክ ለማሰጠት እየሄደች ያለችበት መንገድ የትኛውን አካል የሚጠቅም አይደለም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ይህ እንቅስቃሴ ተገቶ መሬት ላይ ያለውን እውነት መነሻ ያደረገ ወይይትና ድርድር እንዲቀጥል ህብረቱ በጎ ሚናውን ይወጣል ሲሉ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የአፍሪካ ህብረት በአሁን ሰዓት እያከናወነ ያለውን ተቋማዊ ሪፖርት ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ ጠቁመው÷ ለህብረቱም ስኬታማ ጉዞ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

በአዲሱ የሪፎርም ማሻሻያ ሲደረግ በተቋሙ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን መብትና ጥቅምን ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበትም ሚኒስትር ዴኤታው ጠይቀዋል።

የህብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት በበኩላቸው÷ አባይ አፍሪካዊ ወንዝ በመሆኑ አጀንዳው አህጉራዊ መሆን እንዳለበት ህብረቱ እንደሚያምን ገልፀዋል።

ድርድሩም በአፍሪካ ማዕቀፍ እልባት እንዲያገኝ ህብረቱ የማያይቋረጥ ድጋፍ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡

ህብረቱ በሚያከናውነው ተቋማዊ ሪፎርምም የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ባከበረ መልኩ እንደሆነ ማረጋገጣቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version