አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምሕረቱ በህገወጥ ንግድ እና በጸጥታ ችግር ምክንያት ከወርቅ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ በመሆኑ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናገሩ።
የወርቅ ዋጋን ጨምሮ መግዛት ከእርምጃዎቹ መካከል አንደኛው መሆኑን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
የግብይት ስርዓቱን ለማስተካከልም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
አሁን የወርቅ ብቸኛው ገዢ ብሔራዊ ባንክ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል።
አያይዘውም የውጭ ምንዛሬ ተመን ይቀንሳል በሚል የሚሰራጨው ዜናም ሃሰተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕገ-ወጥ ንግድ እና የሰላም ችግር የወርቅ ንግድ አፈጻጸም እንዲቀንስ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ማሞ አንስተዋል፡፡
ብሄራዊ ባንክ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ የባንኩ ቦርድ ትናንት ባደረገው ስብሰባ የወርቅ አቅርቦትን ለማሳደግ የወርቅ ዋጋ ማሻሻሉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት ብቸኛው የወርቅ ገዢ ብሔራዊ ባንክ ብቻ መሆኑን አንስተው÷ሕገ-ወጦችን ለመቆጣጠር ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በአንድ ጊዜ የሚደረግ የተመን ለውጥን አስመልክቶ እስካሁን የተደረገ ውይይትም ሆነ ውሳኔ አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
በህብረተሰቡ ዘንድ አሉባልታ እየተናፈሰ በመሆኑ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እና የዕቃ መያዝ አዝማሚያዎች በመኖራቸው ገበያውን የመረበሽ ሁኔታ መታየቱን አንስተዋል።

