Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግሮች የሠነዱ መጽሐፍት ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግሮች ሠንደው የያዙ “ከመስከረም እስከ መስከረም” እና “ከመጋቢት እስከ መስከረም” የተሰኙ ሁለት መጽሐፍት ይፋ ተደረጉ፡፡

መጻሕፍቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ የተከናወኑ ሁነቶችን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያደረጓቸውን ንግግሮች ሠንደው የያዙ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያየ ጊዜ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ያደረጓቸውን ንግግሮች እና ያስተላለፏውን መልዕክቶች ያካተቱ ናቸው መጻሕፍቱ፡፡

“ቃል ፤ ተግባር፤ ትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ በአብርኾት ቤተ መጻሕፍት እየተካሄደ ያለው የመጽሐፍ ዐውደ ርዕይ እና የውይይት መድረክ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።

ዛሬ ይፋ የተደረጉት መጻሕፍት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ልትሠራ ያቀደችውን፣ የሠራችውን ፣ የገጠማትን ተግዳሮት እንዲሁም ያለፈችበትን መንገድ ለመረዳት የሚያስችሉ መሆናቸውን የፕላንና ልማት  ሚንስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ከያዘው ዕቅድ እና ከገባው ቃል አንፃር ÷ ምን ሠራ? ምን ይቀራል? የሚለውን አንባቢው እንዲረዳ ብሎም እንዲጠይቅ የሚያግዙ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ አበባው አያሌው (ረ/ፕ) ÷ ታሪክ ዛሬ ካልተሠነድ ነገ  የማይገኝ በመሆኑ መጻሕፍቱ የታሪክ ውዝግብን የሚያስቀሩ ናቸው ብለዋል፡፡

መጻሕፍቱ ለታሪክ ጸሐፍት እና ተመራማሪዎች የመጀመሪያ  ምንጭ በመሆን  እንደሚያገለግሉም ነው የጠቆሙት፡፡

 

በትዕግስት አስማማው

Exit mobile version