አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት እና የኢዝላማባድ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ያዘጋጀው የቢዝነስ ጉባኤ ተካሄደ።
በጉባኤው በፓኪስታን ዲፕሎማሲያዊ እና የቢዝነስ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ከንግዱ ማህበረሰብ የተውጣጣው ቡድን ተሳትፏል።
በጉባኤው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዳደረገች ጠቅሰዋል።
የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግ አንዱ እና ዋነኛው የኢትዮጵያ መንግስት የወቅቱ ትኩረት መሆኑን በመጥቀስም የሃገሪቱን አንፃራዊ የተወዳዳሪነት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይበልጥ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ ሃገራት አንዷ የማድረግ አላማ መያዙን አስታውሰው የፓኪስታን ባለሃብቶች እና የንግድ ማህበረሰብ አባላት አዋጭ በሆኑ መስኮች እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የፓኪስታን ንግድ ሚኒስትር ሰይድ ነቪድ ካማር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በንግዱ ዘርፍ ካላቸው እምቅ አቅም አንፃር የሚገኝበት ደረጃ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የንግድ ልውውጡን ለማሳደግ ፓኪስታን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልፀው በሚፈለገው መጠን ለማሳደግ የሁለቱም ሃገራት መንግስታት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል
በጉበኤው የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማህበራት እና የኢዝላማባድ ንግድ እና ኢንዱስትሪ አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈፅመዋል።
እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዘገባ በጉባኤው ተሳታፊ የሆኑ የፓኪስታን ባለሃብቶች እና የንግድ ማህበረሰብ አባላት በተለያዩ ዘርፎች በኢትዮጵያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።