Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰላም ስምምነቱ ትግበራ በተሳካ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ

The African Union logo is seen outside the AU headquarters building in Addis Ababa, Ethiopia, November 8, 2021. REUTERS/Tiksa Negeri

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ስምምነቱ ትግበራ በተሳካ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡

 

የአፍሪካ ህብረት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች የሰላም ስምምነቱን ሂደትና ትግበራው አሁን ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት በመቐለ ከተማ ገለጻ አድርጓል።

 

በገለጻው ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ÷ በስምምነቱ መሰረት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

 

የሰብአዊ እርዳታዎች አቅርቦትና የመሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመር ነዋሪዎችን በእጅጉ እንደጠቀመ ገልጸዋል።

 

ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው ትምህርትም መጀመሩን ጠቅሰው÷ ተማሪዎቹ  ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

 

በመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው፥ ይህ ስኬት የመጣው የፌደራል መንግስትና ህወሓት ለስምምነቱ ትግበራ በቁርጠኝነት በመስራታቸው ነው ብለዋል።

 

በስምምነቱ መሰረት እየተደረጉ ያሉ ትግበራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን እና የሁለቱም አካላት ቁርጠኝነት እምደሚቀጥልም ነው ያነሱት።

 

በመድረኩ ላይ ለተገኙ ወታደራዊ አታሼዎችም÷ ያዩትን ለውጥ ለዓለም ሁሉ እንዲያሳውቁ ጠይቀው ድጋፋቸውንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

 

በአፍሪካ ህብረት የግጭት ማኔጅሜንት ዳይሬክተር አልሃጂ ሳርጆ (ዶ/ር)÷ አሁን ላይ የሰላም ስምምነቱ ትግበራ በተሳካ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

በአፍሪካ ህብረት የመቐለ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሜጀር ጀነራል ስቴፈን ኦ ራዲና ከታህሳስ ወር ጀምሮ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ላይ እየሰራን እንገኛለን ያሉ ሲሆን÷ የአፍሪካ ህብረት ትግበራውን በተመለከት የሚያደርገውን ምልከታ መቀጠሉን አውስተዋል።

 

በትግራይ ክልል አሁን ላይ ከፍተኛ መሻሻል እንዳለ በመጥቀስም የቀድሞ ተዋጊዎችን የማቋቋም ስራው መቀጠሉንና በቀጣይ ሳምንትም የደረሰበትን አጠቃላይ ሁኔታ ምልከታ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።

 

 

በዘመን በየነ

Exit mobile version