Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቋሚ ኮሚቴው የተጀመሩ የሰብዓዊ መብት ማስከበር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተጀመሩ የሰብዓዊ መብት ማስከበር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያሳሰበው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ፥ ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ትምህርትና የግንዛቤ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመስራት በዜጎች ላይ የሚስተዋሉ የመብት ጥሰቶችን መከላከል እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ስራዎቹን በይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በጋራ መስራት በዜጎች ሰብዓዊ መብት ዙሪያ የግንዛቤ ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት፡፡

ሰብሳቢው አክለውም ፥ የተጀመሩ የሰብዓዊ መብት ማስከበር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡

የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተመርምረው ለሚቀርቡ ግኝቶችም የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

በዜጎች ላይ አስገድዶ መሰወር፣ ማሰቃየትና ማሰር የመሳሰሉት ነገሮች እንዲቆሙ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል፡፡

ኮሚሽኑ እየሰራ ያለው ስራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የተቋም ግንባታና ለተቋሙ ሴት ሰራተኞች እያደረገ ያለው ድጋፎች የሚበረታቱ ተግባራት መሆናቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፥ ኮሚሽኑ አበረታች ስራዎችን ቢሰራም ፤ አልፎ አልፎ በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የምርመራ ግኝቶች ላይ የሚቀርቡ ምክረ-ሀሳቦች እንዲተገበሩ ቋሚ ኮሚቴው እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በኮሚሽኑ ነጻ የስልክ መስመር 7307 አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version