Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ 6 ነጥብ 1 በመቶ አድጓል – አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 6 ነጥብ 1 በመቶ አማካይ እድገት ማስመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ተናገሩ፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 24ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡

በመደበኛ ስብሰባው አቶ አሕመድ ሽዴ የ2016 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀትን ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

በማብራሪያቸውም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 6 ነጥብ 1 በመቶ አማካይ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ይህ የሆነውም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች  በተመዘገበው መጠነ ሰፊ  እድገት ነው ብለዋል፡፡

የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም በ2011 በጀት ዓመት ከነበረው 983የአሜሪካ ዶላር በ2014 በጀት ዓመት ወደ 1 ሺህ 218 ዶላር ማደጉን አመላክተዋል፡፡

ሆኖም የኢኮኖሚ እድገቱን በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ በተቀመጠው የ10 በመቶ እድገት ግብ መጠን ማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

ለፉት ዓመታት የነበሩ ተደራራቢ ቀውሶች ይህ ግብ እንዳይሳካ ምክንያቶች ሆነዋል ብለዋል ሚኒስትሩ  በማብራሪያቸው፡፡

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው፣ የወጪ ንግድ አፈፃጸም ከአመታት በኋላ እድገት ማሳየቱም ስኬት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚልኩት ገንዘብ በኮቪድ 19 ከነበረበት ዝቅተኛ አፈፃፀም አሁን ላይ እድገት ማሳየቱንም ነው የተናገሩት።

በመሆኑም የመርቸንዳይዝ የሸቀጦች ወጪ ንግድ ገቢ የ15 በመቶ አማካይ እድገት ማሳየቱን በመጥቀስም በ2014 በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 4 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ለመሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም በ2014 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር መላካቸውን ጠቅሰው፥ የውጭ ሀገር ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ደግሞ በሶስቱ የሪፎርም ዓመታት የ3 ነጥብ 1 አማካይ እድገት ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡

በተደረጉት ሪፎርሞች አብዛኛው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ገቢ እና ትርፍ መጠን ማደጉን እና የኮርፖሬት አመራራቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ተግባራዊ ከተደረጉ ሪፎርሞች ውስጥ በቴሌኮም ዘርፍ መንግስት በብቸኝነት የነበረውን ድርሻ በማንሳት ለግል ዘርፍ ተሳትፎ ክፍት መደረጉን እና በዚህም ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ ለአንድ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያ ፍቃድ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ስራ እንዲጀምር በማድረግ ሀገሪቱ ከዚህ ፍቃድ ተቋም 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንድታገኝ መደረጉን ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ከፍተኛ የእዳ ጫና ያለባላቸውን የመንግስት የልማት ድርጅቶች እዳ የሚረከብ እና የሚያስተዳድር የእዳ እና ሃብት ኮርፖሬሽን ተቋቁሟል ብለዋል።

የመንግስት ግዢ ስርዓትን በማዘመን ቀልጣፋ፣ ግልፅና ውጤታማ ግዢዎችን ለማከናወን የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስርዓት ለምቶ መጠናቀቁን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የፋይናንስ አካታችነት እያደገ መምጣጡን ጠቁመው÷ ለዚህም ዲጂታል ፋይናንስ መስፋፋት ጉልሕ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የባንኮች የተቀማጭ ሂሳብ እና የብድር ገንዘብ ጭማሪ ማሳየቱን እና በተለይም የዲጂታል እና የሞባይል የፋይናንስ አገልግሎን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡

የተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና መብት ተፈቅዶ በሰራ ላይ ለማዋል እንቅሰቃሴ መጀመሩን፤እንዲሁም በሸሪኣ ላይ የተመሰረቱ የፋይናንስ አገልግሎቶች በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡

የካፒታል ገበያን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመላክተው፤በኢንቨስትመንት እና ንግድ ዘርፎች የተደረጉ ማሻሻያዎች የኢንቨስትመንት ማዕቀፍን ለማዘመን ረድተዋል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት በወሰዳቸው እርምጃዎች በርካታ አዎንታዊ ውጤቶች ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ ሀገሪቱ የገጠማትን የበጀት ጉድለት ለመሙላት የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ከማሻሻል በተጨማሪ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርት ጥራትና መጠን መጨመር እንደሚገባ ጠቁመው ÷ለዚህም አስቻይ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ መግባታቸው ገልጸዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመት የምርትና ምርታማነት አለመመጣጠንና የተፈጠረውን የዋጋ ንረት እና የበጀት ጉድለቱን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

 

በፌቨን ቢሻው
Exit mobile version