አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጥ እና ህግ የማስከበር እርምጃ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሰላምን ማረጋገጥና ህግ የማስከበር እርምጃ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ግጭትና ጦርነት የዜጎችን ደህንነትና ነጻነት አደጋ ላይ በመጣልና ዴሞክራሲን በማወክ የሰው ህይወትና ንብረት ያጠፋሉም ነው ያሉት።
ሰላም በሌለበት ብልጽግናን ማረጋገጥ ስለማይቻል ሰላምን ለማረጋገጥ በተደመረ አቅም መስራት እንደሚገባ ያነሱት ሚኒስትሩ፥ የሰላምን ቀጣይነት ማረጋገጥና ማፅናት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የሰላም በሮች ለሁሉም ሃይሎች ክፍት መሆናቸውን ተከትሎም በሀገሪቱ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንም አስረድተዋል።
የሰሜኑ ግጭትም በፕሪቶሪያው እና የናይሮቢው ስምምነት መሰረት በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት በስኬት እየተፈጸመ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ልትሆን እንደሚገባት ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያ ዕድገቷ የተረጋገጠ እና በቀጠናው ብሎም በአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ትሆናለች ብለዋል።
ከሸኔ ጋር የተጀመረው ሰላም የማስፈን ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጥቀስም፥ በቤኒሻንጉል እና በጋምቤላ የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎችም በተከፈተው የሰላም በር መጠቀም በመቻላቸው አካባቢዎቹ የተረጋጉ እና ሰላማቸው የተረጋገጠ መሆን መቻሉን አንስተዋል።
መንግስት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን፣ የግዛት አንድነትን እና ህብረ ብሔራዊነትን ለሚያረጋግጥ ሰላም ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ እንደማያስቀምጥም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ሰላምን ለማጽናት እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመጠበቅ አንድ ሀገራዊ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ የመገንባት ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
በክልሎችም የተቀናጀ ወንጀሎችን መከላከል የሚችል የተጠናከረ መደበኛ ፖሊስ የመገንባት ስራ በተሳካ መልኩ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ሰላምን የተሻለ ለማድረግ ቂምን መሻር እና ከሂሳብ ማወራረድ እሳቤ በመውጣት የሽግግር ፍትህን ለማስፈን የተጀመረው ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ማህበረሰቡም የሰላም ማስፈኑን ሂደት እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።