Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል – ሙሳ ፋኪ ማህማት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ -መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማትገለጹ።

14ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪዎች ጉባዔ በጅቡቲ እየተካሄደ ነው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካን ቡድናቸው በጉባዔው ላይ እየተሳተፈ ነው።

በጉባዔው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት÷በሱዳን የተከሰተው ግጭት አሁንም መቀጠሉንና ዜጎች ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የሕብረቱ አባል ሀገራት እና ዓለም አቀፍ አጋሮችን ያካተተ አሰራር ዘርግቶ ሰላም እንዲመጣ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አመላክተዋል።

ሱዳን በሲቪል የሚመራ ሽግግር ለማምጣት ያለው ሂደት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሏ ከቀናት በፊት ከአፍሪካ ሕብረት አባልነት መታገዷንም ጠቅሰዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሃና ሰርዋ ቴቴ በበኩላቸው÷ተመድ የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላም ለማምጣት በዘረጋው አሰራር አማካኝነት ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እና በሶማሊያ የተካሄደውን ስኬታማ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመልካም ስራ ውጤት ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ተመድ በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላም እና ልማት እንዲመጣ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ልዩ መልዕክተኛው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉ ዓለም አቀፍ አጋሮች÷ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ልማትን ለማምጣት የተጀመሩ ጥረቶች መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ለአንድ ቀን በሚቆየው 14ኛው የኢጋድ የመሪዎች ጉባዔ የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች እና ባለስልጣናት እየተሳተፉ ሲሆን÷ ተቋሙ በምስራቅ አፍሪካ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች እየሰጠ ያለውን ምላሽ ጨምሮ በተለያዩ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ተገልጿል።

 

Exit mobile version