አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ፈጠራ በቀውስ ጊዜ” በሚል ርእስ የአዲስ ወግ ዌቢናር በቴክኖሎጂ በመታገዝ በቪዲዮ ኮንፍራንስ ተካሄደ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሲዘጋጅ የቆየው የአዲስ ወግ አንድ ጉዳይ በቪዲዮ ኮንፍረንስ/ዌቢናር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያመጣውን ተከትሎ ለመጻዒ ፍላጎቶች እና ፈተናዎች ፈጠራ የታከለበት መፍትሔ ማፈላለግ ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ ምክክር አድርጓል።
ዌቢናሩ ላይም የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የታሪክ ምሁር ዶክተር ታምራት ሀይሌ፣ አቶ የሱፍ ረጃህ ከኢትዮ ጆብስ የስነ ልቦና ባለሙያ ሰብለ ሀይሉ እና አቶ ቴድሮስ ታደሰ ተካፍለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሰክረተሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን፥ ፈተናዎች እና ቀውሶች በሚያጋጥሙ ጊዜ ፈጠራዎችን መጠቀም የግድ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ፈተና ሲያጋጥሙ ቀደምት አባቶች ፈጠራዎችን ተጠቅመው አልፈዋል ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በዛሬው መድረክም እኛም በዚህ የፈተና ወቅት ፈጠራን እንዴት ተጠቅመን ማለፍ አለብን የሚለው ላይ ይደረጋል ብለዋል።
ዌቢናሩ አወያይ የሆኑት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ፥ በዚህ ቀውስ ወቅት ፈጠራዎችን መጠቀም የግድ መሆኑን አንስተዋል።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፥ ፈጠራ ሁል ጊዜ አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ አይነት ቀውስ በሚከሰትበት ወቅት ደግሞ በልዩ ትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኮቪድ – 19 ወረርሽኝን አስመልክቶ እስካሁን በርካታ ጥረቶች እየተደረገ ነው ያሉ ሲሆን፥ ሀገራትም በየፊናቸው ጥረት እያደረጉ ነው፤ ነገር ግን በዘርፉ ትብብር እንደማይስተዋል አንስተዋል።
በጋራ የመጣን ወረርሽን በጋራ መመከት ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፥ እንዲህ አይነት ወረርሽኝን በአሸናፊነት ለመወጣት የሚቀርብ ፈጠራ ብልሃት የተሞላበትና ችግር ፈቺ ሀሳብ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የአሁኑ ወቅት ፈጠራ መጀመሪያውና መጨረሻው ህይወትን ማዳን እንዳለበት በመጥቀስ፤ ይህም ፈጠራዎቹን ከሌላ ጊዜ ለየት እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።
ፈጠራዎቹ አብሮነትን የሚያጎሉ፣ ሀገርን የሚጠብቁ እና ከፍ የሚያደርጉ እንዲሁም ሰብአዊነትን፣ ሙያዊ ስነ ምግባርን፣ የሰዎችን ማንነት፣ ሀይማኖትን እና ባህልን ያከበሩ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም አስታውቀዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የታሪክ ምሁር ዶክተር ታምራት ሀይሌ በዓለማችን ላይ በተለያዩ ጊዜያት የበርካቶችን ህይወት የቀጠፉ ወረርሽኞች መከሰታቸውን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ቀውሶች ሲከሰቱ የሰው ልጆች እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፤ ቀውሶችን ለማሸነፍ እና ከዚያ በኋላም ኑሮን ለማስቀጠል ፈጠራዎችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያም በተለይም በህዳር ወረርሽን ወቅት ለሰዎች በቤታቸው ምግብ የማድረስ እና በቀብር ወቅት በሽታው ወደሰው እንዳይተላለፍ የተወሰዱ እርምጃዎችንም በማሳያነት አንስተዋል።
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋም፥ በቀውስ ወቅት የሀገሪቱን አሰራር መፈተሽ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቀውስ ሲከሰት የሚከታተል እና የመከላከል ስራን የሚሰራ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አላት ያሉት ዶክተር ፍፁም፥ ይሁን እንጂ አሁን ያለውን ወረርሽን ለመከላከል በድርቅ ወቅት ከሚከተለው አሰራር ጋር ተመሳሳይ መሆን የለበትም፤ አዲስ አደረጃጀት እና አሰራር ለመከተል በጥናት በመታገዝ እየተሰራበት ነው ብለዋል።
ዶክተር ፍፁም አክለውም፥ ቴክኖሎጂን በቀውስ ጊዜ መጠቀም ላይ የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም አሁንም በርካታ ቀሪ ስራዎች እንዳሉም አስታውቀዋል።

