አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርናው ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ከፍተኛ ሚና ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)ገለፁ።
ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ብሔራዊ ባንክ በጋራ ያዘጋጁት የግብርና ፋይናንስ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በግብርናው ዘርፍ አሁንም ያልተነኩ እምቅ ሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ያለውን ከፍተኛ የውሃ፣ የመሬት እና የሰው ሃብት በመጠቀም የተሻለ ማምረት እንደሚገባም ገልጸዋል።
መንግስት የግብርናው ዘርፍ እንዲዘምን በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን በመጥቀስም፥ ለሜካናይዜሽን የሚያገለግሉ ከ500 በላይ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መደረጉን አንስተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግስት ለዘርፉ ዕድገት እየሰራ ቢሆንም የፋይናንስ ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ የሚያቀርቡት ብድር አሁንም አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት ያለውን ከፍተኛ ሚና ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ አቅርቦት ፈሰስ ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው፥ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ መውጣቱን ነው የተናገሩት።
ባንኮችም የፋይናንስ አቅርቦታቸውን ለማጠናከር አዋጁን በአግባቡ መተግበር እንዲጀምሩ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡