አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ውሃ መያዝ የሚችልበት የግንባታ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንዳሉት የግንባታ ሥራው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባወጣው የጥንቃቄ መመሪያ መሰረት እየተከናወነ ነው።
የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት የሚያስችላቸውን ውሃ በመጭው ክረምት ለመያዝ የሚቻልበት የግንባታ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፥ የግድቡ ኃይል ማመንጫ ዩኒት 9 እና 10 ግንባታ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ግድቡ ኃይል እንዲያመነጭ ከታሰበው ጊዜ በላይ ከተራዘመ በየዓመቱ መገኘት ያለበትን ገቢ ከማሳጣቱም ባለፈ ለተጨማሪ የግንባታ ወጪ ይዳርጋል ያሉት አቶ ሞገስ፥ አላስፈላጊ ወጪን ለማስቀረትም በዕቅዱ መሰረት የውሃ ሙሌት ሥራው ከዘንድሮው ክረምት እንደማያልፍ አስረድተዋል።
ግድቡ ክረምት ላይ ውሃ መያዝ ከቻለ ከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ በኋላ ሁለቱ ኃይል ቀድመው የሚያመነጩ ዩኒቶችን በመፈተሽ ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአሁኑ ጊዜ የግድቡ የብረታ ብረት ሥራ 26 በመቶ ላይ ደርሷል፤ ይህ አሀዝ የዛሬ ሁለት ዓመት ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ጥራትና ግብዓት እንደ አዲስ እርማት ተደርጎለት ግንባታው እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የብሔራዊ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢና የሦስትዮሽ ድርድር ኮሚቴ አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው፥ ግድቡ 65 ሜትር ቁመት ላይ ሲደርስ የመጀመሪያ ዙር ውሃ የመሙላት ዕቅድ መያዙን ገልጸው ይህም በተያዘው ዕቅድ መሰረት በዘንድሮው የዝናብ ወቅት እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የውሃ ሙሌቱ በየዓመቱ ደረጃ በደረጃ የሚከናወን ሲሆን፥ የግድቡ ተርባይኖች ሙሉ ለሙሉ ኃይል ማመንጨት የሚችሉበት ቁመት ላይ እስከሚደርሱ ውሃው ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ይሞላል ብለዋል።
የግድቡን ውሃ ሙሌት በሁለት ዓመት ማከናወን ቢቻልም የግድቡን ደህንነትና የታችኞቹ ተፋሰስ ሃገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ላለማድረስ ደረጃ በደረጃ የመሙላት እቅድ መያዙንም አውስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም በአሁኑ ወቅት 73 በመቶ መድረሱን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

