Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲሱን የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ መረቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ አበባ በተለምዶ ሸጎሌ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የተገነባውን አዲሱን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ሚዲያ ኮምፕሌክስን መርቀው ከፍተዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷መገናኛ ብዙሃን የሕዝብን ችግር የሚያንጸባርቁ አጀንዳዎችን መፍጠር አለባቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ልዕልና ከፍ የሚያደርጉ ሃሳቦችን የሚያነሱ እና መንግስት ሲያበላሽ የሚጠይቁ መሆን እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡

መገናኛ ብዙሃን የሚነገርን ድምጽ የሚያጎሉ ሰይሆን ድምጽ የሚፈጥሩ መሆኑን እንደሚገባቸውም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በሚዲያው ዘርፍ የሚሰሩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ከሰፈር ሽኩቻ በመውጣት በቀዳሚነት የሕዝብ ድምጽ መሆን አንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

አዲሱ የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ዓለም በደረሰበት የሚዲያ ቴክኖሎጂ የተደራጁ ስቱዲዮዎች ያሉት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ኢቢሲ “ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ቃል በሁሉም አማራጮቹ አዳዲስ ይዘቶችን እና አቀራረቦችን አካቶ ወደ አድማጭ ተመልካች ለመድረስ ዝግጅት ማጠናቀቁንም አስታውቋል፡፡

የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ በበኩላቸው ÷ ተቋሙ ኢትዮጵያ ቁልፍ የታሪክ ሽግግር በምታደርግበት ምዕራፍ እና በነገ የትውልድ ግንባታ ውስጥ ከትናትንትም ሆነ ከዛሬ የላቀ ሚና መጫዎት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ግዙፍ ታሪኮች ባለቤት ናት ያሉት አቶ ፍስሃ÷ ኢቢሲም በቀጣይ ሊነግርን እና ሊያሳውቀን የሚገባው ብዙ ስራዎች እንዳሉ አንስተዋል፡፡

ዴሞክራሲን ለማስፈን እና ለማጽናት የሚያስፈልገውን የሃሳብ ብዝሃነት ለማንጸባረቅም ግዙፍ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version