አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዚህ አመት 7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ቢያንስ 6 ነጥብ 1 በመቶ እንዲሁም በሚቀጥለው ዓመት 6 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ታሳያለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም ትንበያ ጠቅሰው ገልጸዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን እድገት እያመጡ ካሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ዓመት 7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ይመጣል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ እምርታ እየታየ መሆኑን በማንሳትም ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ 33 በመቶ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ሃገር በቀል ማሻሻያ ዕቅድ ቀላል የማይባል እምርታ ማምጣቱንም ነው ያነሱት።
መጀመሪያው ሃገር በቀል ማሻሻያ ዕቅድ የግሉን ዘርፍ ማነቃቃት ፣በማክሮ ኢኮኖሚ የተፈጠሩ ስብራቶችን መጠገን ፣ ምርታማነትን በብዝሃ ዘርፍ ማብዛት እና የሃገርን እድገት ማስቀጠልን እንደ ዋና ግብ አድርጎ መነሳቱን አንስተዋል፡፡
ይህ እቅድ በርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች ፈተና እንደሆኑበት በመጥቀስም፥ ሆኖም የመጀመሪያው ሃገር በቀል ማሻሻያ ዕቅድ ቀላል የማይባል እምርታ አግኝተንበታል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
“ነገር ግን ሙሉ በሙሉ የያዝነውን እቅድ አሳክተን የምናስበውን ሰላም እና ምርታማነት ለማምጣት የነበርንበት ሃገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ምቹ ባለመሆናቸው ሁለተኛውን ሃገር በቀል ማሻሻያ ዕቅድ አዘጋጅተናል” ነው ያሉት በማብራሪያቸው።
ከነገ በስቲያ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የሁለተኛው ሃገር በቀል ማሻሻያ ዕቅድ፥ የኢኮኖሚ ስብራቶችን መጠገን ፣ እድገትን ማስቀጠል እና ለህዝቡ የተገባውን ቃል የማሳካት አላማዎችን ያነገበ መሆኑንም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የዋጋ ንረት የኢኮኖሚው ዘርፍ ከፍተኛ ፈተና መሆኑን ገልጸው ይህም ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን አንስተዋል፡፡
አጠቃላይ የዋጋ ንረት 37 በመቶ ደርሶ የነበር መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በዘንድሮው በጀት ዓመትም የገንዘብ አቅርቦትን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እንደሚሰራ ፤ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ገንዘቦችን መቆጣጠርም ሌላኛው ስራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር )ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ የኢትዮጵያ እዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት 38 በመቶ ደርሷል፤ ይህንንም ሳናቋርጥ እየከፈልን ነው፤ በቀጣይ ከ30 በመቶ በታች ለማድረግ ይሰራልም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት 11 ወራት 365 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለፈው ዓመት አንጻር 26 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ማሳየቱን አንስተዋል፡፡
ከወጪ አንጻር ደግሞ ባለፉት 11 ወራት 574 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን እና ከአምናው አንጻር 13 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው