አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በጤናው ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ሲሉ የአፍሪካ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር (የአፍሪካ ሲ ዲ ሲ) ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ዢን ካሴያ ገለጹ፡፡
በዶክተር ዢን ካሴያ የተመራ የሲ ዲ ሲ አመራሮችና ሰራተኞች ቡድን ሀገር አቀፉን የጤና ዐውደ-ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም መጎብኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የጤና ዐውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየሰራች ያለውን ውጤታማ ስራ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ዶክተር ዢን ካሴያ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በጤናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች በዐውደ ርዕዩ በመመልከታቸው ተደንቀው÷ ሌሎች ሀገራትም ሊመለከቱት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ÷ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አተገባበር፣ በዲጂታል ጤና ስርዓት መዳበር፣ አዳዲስ የሕክምና መገልገያ ዕቃዎች በሀገር ውስጥ በማምረት እና በጤና ተቋማት አገልግሎት አደረጃጀት እንዲሁም ቅብብሎሽ ስርዓት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የጤና ዐውደ ርዕይ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ቢጎበኙት÷ ሀገራቱ ብዙ ልምድ እንደሚያገኙ አስገንዝበዋል፡፡