Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል- አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ÷ የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ የጀርመን ልዩ መልዕክተኛ ጄኒፈር ሊ ሞርጋን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን እና የካርቦን ልቀት መጠንን መግታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መክረዋል፡፡

በተጨማሪም በታዳሽ ኃይል እና በኢትዮጵያ የተጀመረውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለማስቀጠል በትብብር መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን÷ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል በርካታ እርምጃዎች መውሰዷን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታላቁ ኅዳሴ የኤሌክትሪካ ኃይል ማመንጫ ከአየር ብክለት ነጻ የሆነ ታዳሽ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ-ንዋይ እያፈሰሰች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛዋ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጀመረችው የአረንጓዴ የሻራ መርሐ-ግብር እንዲሳካ ጀርመን ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነች መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version