አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ግጭቱን በማቆም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደርሱ አሳሳበ።
ኢጋድ የሱዳንን ግጭት ለመፍታት ያቋቋመውን የአራትዮሽ የመሪዎች ስብሰባ ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ አካሂዷል።
ስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ የተመራ ሲሆን፥ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገራት እና የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል።
ድርጅቱም ከስብሰባው በኋላ ባወጣው መግለጫ የሀገሪቱ ተፋላሚ ሃይሎች ግጭቱን በማቆም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ዘላቂ የተኩስ አቁም ሊደርሱ እንደሚገባ አስገንዝቧል።
ከዚህ በፊት የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተደርሰው መጣሳቸውን ያነሳው የኢጋድ መግለጫ፥ የሚደረሰው የተኩስ አቁም የመተግበሪያ ዘዴ ሊበጅለትና ክትትል ሊደረግበት እንደሚገባም አስገንዝቧል።
አሁን በሱዳን ያለው ሁኔታ በውጭ ጣልቃ ገብነት ምክንያት እየተራዘመና እየተባባሰ መምጣቱንም በመግለጫው አንስቷል።
ወታደራዊ አማራጭ ለሱዳን መፍትሄ አይሆንም ያለው የኢጋድ መግለጫ፥ ተፋላሚ ሃይሎችን ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል።
ድርጅቱ በመግለጫው በሱዳንት ግጭት በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን እና 3 ሚሊየን ዜጎች በሀገር ውስጥና ወደ ጎረቤት ሀገራት በስደት መፈናቀላቸውን ጠቅሶ ሁኔታው እንዳሳሰበው ገልጿል።
አሁን ላይ በሱዳን ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዳሳሰበው ያነሳው መግለጫው፥ ግጭት በተከሰተባቸው የሱዳን አካባቢዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሕዝቡ ይደርስ ዘንድ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወሰድ ወስኗል፡፡
በተለይም በግጭቱ ይበልጥ ተጋላጭ የሚሆኑት ሴቶች ፣ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞች እንደመሆናቸው መጠን የበለጠ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያለው።
የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመታደግ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል በሱዳን መስፈር በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዲመክር እና ከሱዳን ጋር የሚጎራበቱ ሀገራትም ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረስ ረገድ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የይለፍ ፈቃድናን የጉሙሩክ አገልግሎቶችን ጨምሮ ለሱዳን በሚደረጉ የሰብዓዊ አቅርቦት ድጋፎች ላይ እክል የሚሆኑትን ማናቸውንም እንቅፋቶች እንዲያቀሉም ጠይቋል፡፡
በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ፣ አስገድዶ የመድፈር ሁኔታዎችን እና አሁንም የቀጠሉ ግጭቶችን በጥብቅ አውግዟል፡፡
እንደዚህ ባሉ ሁኔታዎች ላይ ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ አቋም ይዟል፡፡
የሱዳንን ሕዝብ እና የሀገሪቷን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ማናቸውንም እርምጃዎች ለመውሰድ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው መግለጫው ያመላከተው፡፡
የሱዳንን ሕዝብ የዘላቂ ሠላም ፍላጎት ለማረጋገጥም የግጭቶችን መነሻ ከሥር መሠረቱ ለመፈተሽ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አካታች የሆነና በሱዳናውያን የሚመራ ሀገር አቀፍ ውይይት እንዲያካሂዱም ነው የጠየቀው፡፡
አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ “ኢጋድ ከአፍሪካ “ኅብረት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራ መግለጫው አመላክቷል፡፡
የስብሰባው ተሳታፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሱዳንን ግጭት ለመፍታት የተቋቋመውን የአራትዮሽ የመሪዎች ስብሰባ በማስተናገዳቸው እና ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት እና ኢጋድ በሱዳን የተከሰተው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የጋራ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት እያከናወኑት ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል።
መግለጫው አያይዞም የሱዳንን ግጭት ለማስቆም እና በሲቪል አስተዳዳር የሚመራ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የኢጋድ አባል ሀገራት የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አመላክቷል።
ኢጋድ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች የሱዳንን ግጭት ለመፍታት በተካሄደው የአራትዮሽ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመገኘት ማረጋገጫ ባለመስጠታቸውም ሆነ ባለመገኘታቸው ቅር መሰኘቱን በመግለጫው አንስቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ሌሎች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እያደረጉት ላለው ጥረት እውቅና ተሰጥቷል፡፡
በሱዳን ባለው ግጭት ምክንያት ድንበር አቋርጠው ለገቡ ሱዳናውያን በራቸውን ክፍት አድርገው ከለላ ለሰጡ ጎረቤት ሀገራትም ድርጅቱ ምስጋናውን አቅርቧል።