Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን ባለመጉዳት ቃሏን የምትጠብቅ ናት – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስ እህት ሀገራትን ለመጉዳት የማታስብና ቃሏን የምትጠብቅ ሀገር ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ታማኝነት እና የገቡትን ቃል መፈጸም የኢትዮጵያውያን በጎ ባህሪያት እና የባህላችን ዋነኛ አካል ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ መተማመንን ችላ የማትል እና ጎረቤቶቿን ለመጉዳት የማታስብ ሀገር መሆኗን እናረጋግጣለን ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ዓባይ የላይኛውንና የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ለሺህ ዓመታት ያስተሳሰረ ገመድ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው፡፡

ይህን ከፈጣሪ የተሰጠ ገጸ በረከትም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለማልማት እና ለመጠቀም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍላጎት አላት ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም የዓባይ ወንዝ ከልማትና ከተለያዩ ጥቅሞች ባሻገር የተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦችን አስተሳስሮ መቆየቱንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

“ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ተከታዮቻቸውን ሰላም ወደሰፈነባት የሐበሻ ምድር ሂዱ፤ ንጉሳቸውም ማንንም የማይጨቁን ነው” ያሉትን ያስታወሱት ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ማንንም የማትጎዳና ያላትን በማካፈል በአብሮነት ለማደግ የምትጥር ሀገር መሆኗን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፍላጎት የተፋሰሱ ሀገራትን ያማከለ ብልጽግና ለማምጣት በጋራ መስራት መሆኑንም ነው ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በአጽንኦት የገለጹት፡፡

እንዲሁም የጋራ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ትብብርን ማሳደግ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ግብጽን ጨምሮ የተፋሰሱ ሀገራትን የመጉዳት ሐሳብ ኢትዮጵያ እንደሌላት በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህም የፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጥበብ የተሞላበት አመራር እና ግብጽን ለመገንባት እና ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ግብጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሁሉም ከፍተኛ ጥቅም አለው ብለው እንደሚያምኑም ጠቁመዋል፡፡

ከልማታዊ ፋይዳዎቹ መካከልም የዓባይን ውሃ የትም ቦታ ቢሆን በበቂ ሁኔታ በማጠራቀም ለተለያዩ ጥቅሞች ማዋል አንዱ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

እንዲሁም በአስቸጋሪ ወቅቶች ለሚያጋጥሙ እንደ ድርቅ ላሉ አደጋዎች ዋስትና መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ለሕዝቦች የጋራ እና ቀጣይነት ያለው ልማት ተባባሪና ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)÷ አሸናፊውም ይኸው ሐሳብ መሆኑን በመልዕክታቸው አስረድተዋል፡፡

Exit mobile version