Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የ36 ሚሊየን ዶላር ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የ36 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ የበጀት ስምምነት በመንግሥት እና በአጋር ድርጅቶች መካከል ተፈርሟል።

ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ  ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከአጋር ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተፈራርመዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ÷የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንደ ሀገር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እስከ ጤና ኤክስቴንሽን  መዋቅር  ድረስ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም አገልግሎቱን እየፈለጉ ተደራሽ ያልሆኑ 22 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች መኖራቸውን ነው የገለጹት፡፡

የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማጠናከር እንቅፋት ከሆኑ ተግዳሮቶች መካከል  ወጪው አብዛኛው  በለጋሽ አካላት የሚሸፈን በመሆኑና የለጋሽ አካላት ድጋፍ በተለያየ ምክንያት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረት በመኖሩ ለግብዓት የሚያስፈልግ የበጀት ዕጥረት ማጋጠሙን ጠቁመዋል፡፡

የአቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍም በመንግሥት እና በአጋር አካላት የ36 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ የበጀት ስምምነት እንደተፈረመ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version