Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ተፅፎ የማያልቅ ታሪክ ያለው ዕዝ ነው – ጄ/ል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ እና የሪፐብሊካን ጥበቃ ሃይል የሠራዊት አባላት ለኢትዮጵያ በከፈሉት ዋጋ ተፅፎ የማያልቅ ታሪክ ያላቸው መሆኑን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ይህንን የገለፁት የሁለቱ ክፍል አመራሮች በጋራ ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ ባደረጉበት ዕለት ነው።

በውጊያ የበላይነት ለመያዝ ሁሌም የማያቋርጥ የሃይል ዝግጅት ማድረግ እና የሞራልና የሐሳብ የበላይነት በመያዝ በጠንካራ ወታደራዊ ሳይንስ ሁሉንም አደረጃጀቶች አቀናጅቶ መምራት ለድል አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው ብለዋል።

ጄኔራል አበባው የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ እና የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል ውጊያዎችን በማረም፣ በማስተካከል እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቀየር ወደር የሌለው ውጤት ማስመዝገባቸውን አውስተዋል፡፡

ወታደር ካለፈ ታሪክ ይማራል እንጂ ባለፈ ታሪክ አይኖርም፤ ስለዚህ ካለፈው ታሪካቸው በመማር ሁለቱም ክፍሎች ለላቀ ድል መዘጋጀት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

ሁለቱም ክፍሎች ያስመዘገቡት ውጤት ከላይ እስከታች ባለው የአመራሩ እና የአባላቱ ጠንከራ ቅንጅት የተገኘ ድል እንደሆነ መናገራቸውንም የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

ስለሆነም ይህንን ጥንካሬ እና የተናበበ ቅንጅት በመጠበቅ ተፅፎ በማያልቀው ታሪካቸው ላይ ተደማሪ ታሪክ ለመፃፍ ሁሌም ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ እንዲሁም መንግስት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የላቀ ክብር እንዳላቸው በመግለፅ÷ ሠራዊቱም የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በፅናት እየተወጣ እንደመጣው ሁሉ አሁን ላይም የሚሰጠውን ሀገራዊ ግዳጅ በውጤት መፈፀም እንደሚገባው አሥገንዝበዋል።

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው÷ የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ በየደረሱበት ሁሉ ሁኔታዎችን በፍጥነት በመቀየር ሀገርና ህዝብን ያኮራ ታሪክ መፈፀሙን ገልፀዋል።

Exit mobile version