አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎቻቸው ቢያንስ 25 በመቶዎቹን ማሳለፍ ካልቻሉ የትምህርት መስኮቻቸው እንዲታጠፉ የሚያስገድድ መመሪያ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።
የትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጿል።
በባለስልጣኑ የከፍተኛ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ክትትል እና ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ከፍያለው አድነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ የመማር ማስተማር ስራው ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን አዲስ መመሪያ እና መስፈርት ተዘጋጅቷል።
የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት የሚጠበቀውን ደረጃ እና ጥራት ማስጠበቅ ያስችላል የተባለው አዲስ መመሪያ እና መስፈርትም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት።
በመመሪያው የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ በርካታ መለኪያዎች የተቀመጡ ሲሆን፥ አንዱ የመውጫ ፈተናን የሚመለከት መሆኑንም አስረድተዋል።
በዚህም እያንዳንዱ ተቋም ለመውጫ ፈተና ከሚያስቀምጣቸው ተማሪዎች በየትምህርት መስኩ ቢያንስ 25 በመቶዎቹ ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው በማንሳት ይህ ካልሆነ ግን የትምህርት ፕሮግራሙ ይሰረዛል ብለዋል።
በተጨማሪም የትምህርት ተቋማቱ ለማስተማር የሚመዘግቧቸውን ተማሪዎች ለባለስልጣኑ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው ተብሏል።
ዘንድሮ በተሰጠው የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተና ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተናውን ከወሰዱ 72 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት 50 እና ከዛ በላይ ያመጡት 12 ሺህ 422 ወይም 17 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ መሆናቸው ይታወቃል።
በዙፋን ካሳሁን