Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሞሮኮ ከኢትዮጵያ ጋር በባንክና ሌሎችም መስኮች በትብብር እሰራለሁ አለች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሞሮኮ ከኢትዮጵያ ጋር በባንክና ሌሎችም መስኮች በትብብር እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኔዛ አሎዩ ምሃምዲ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኔዛ አሎዩ ምሃምዲ፥ የሁለቱ ሀገራት ዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮች በውጤታማነት መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

የሞሮኮው ንጉስ መሃመድ ስድስተኛ በፈረንጆቹ 2016 በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድርጋቸውን ተከትሎ ሀገራቱ 16 የአጋርነት ሥምምነቶችን በመፈራረም ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በዚህም የኢትዮጵያና ሞሮኮ ወዳጅነትና የትብብር ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን አምባሳደሯ ተናግረዋል።

በተለይም በግብርና፣ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚ ትብብር መስኮች አገራቱ በጋራ እየሰሩ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቀጣይነትም በእነዚህና በሌሎች መስኮች ሞሮኮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለችም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በተሳካ መልኩ በውጤታማነቱ ቀጥሏል ያሉት አምባሳደሯ ፥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር በባንክና ሌሎችም መስኮች በትብብር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ስትራቴጂክ አጋርነት መጠናከሩን የገለጹት አምባሳደር ኔዛ አሎዩ ፥ ከግብርና፣ ንግድና ኢንቨስትመንት በተጨማሪ በስፖርት ዘርፍም በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

በዓለም ስመ ጥር የሆኑ አትሌቶች መፍለቂያ ከሆነችው ኢትዮጵያ፤ ሞሮኮ ልምዶችን መጋራት ትሻለች ያሉት አምባሳደሯ ፥ ሞሮኮም በእግር ኳስ የካበተ ልምዷን ለኢትዮጵያ ታጋራለች ሲሉም ነው የተናገሩት።

በቀጣይ ይካሄዳል ተብሎ የሚታሰበው የኢትዮ-ሞሮኮ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ከማጠናከር ባለፈ የሥምምነት ማዕቀፎችን አፈፃፀም የሚገመግሙበት ይሆናል ተብሏል።

የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቅርቡ በኬኒያ ከተካሄደው 43ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈፃሚዎች መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።

Exit mobile version