አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአማራ ክልል እየተስተዋሉ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ገለፁ፡፡
አቶ ደመቀ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እና ችግሮችን ለመፍታት ጠቃሚው መንገድ ሰላማዊና የውይይት አግባብ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ከውይይት ውጭ ያለው አካሄድ÷ የጥያቄዎችን መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ ፣ ያለንን የሚያሳጣ፣ በዘላቂነት ሊታዩ ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች ሁሉ እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ አካሄድ ነው ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
‘ሰላም ከሌለህ ሁሉን ታጣለህ’ የሚባለውን እውነታ ከልብ በማጤን በአስተውሎት መጓዝ በሚገባን ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡
በየዘመኑ ፈተናዎች እና ችግሮች ሲገጥሙ በጥበብ ተሻግረው ያሻገሩንን የአባቶቻችን ጥበብና አስተውሎት ማጥበቅ እንደሚጠይቅም ነው ያስረዱት፡፡
የሀገር ሽማግሌ የጠፋበት፣ ታላቅ የሌለበት፣ መካሪ የሃይማኖት አባት የታጣበት ይመስል ሁላችንንም የሚያባላና የሚበላ አካሄድ ይስተዋላል ሲሉም አንስተዋል፡፡
የዚህ መጨረሻ በግራም በቀኝም ከውጭም ከውስጥም ላሰፈሰፉ ኃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖ አቅም የሚያሳጣ፣ ክብራችንን የሚጎዳ፣ ተጋላጭነታችንን የሚያሰፋ በአጠቃላይ ሁሉንም የሚያሳጣ እንዳይሆን ያሰጋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ከለውጡ ብዙ የተጠበቁ ነገር ግን ምላሽ ያልተገኘባቸው ያላረኩ እና ሌሎች ችግሮችና ስሜቶች ይኖራሉ ያሉት አቶ ደመቀ÷ ለእነዚህ ጉዳዮች ቆም ብሎ በማሰብ በሰላሙ መንገድ ዘላቂ መፍተሄ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም የሁሉም ዋስትና የሆነውን ሕግና ሥርዓት በተሟላ መልኩ ማክበርና ማስከበር እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!