Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፋና በማህበረሰብ አገልግሎት ለትምህርት ቤት እድሳት የሚውል 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በማህበረሰብ አገልግሎት በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ ገላን አራብሳ ወረዳ ለቢሊ ሲልጦ ቡኡራ ቦሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እድሳት ግንባታ የሚውል 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አመራር እና ሰራተኞች ዛሬ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም አካሂደዋል፡፡

ተቋሙ በሸገር ከተማ ኮዬ ክፍለ ከተማ ገላን አራብሳ ወረዳ ቢሊ ሲልጦ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በመገኘት ለቢሊ ሲልጦ ቡኡራ ቦሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እድሳት ግንባታ የሚውል 2 ሚሊየን ብር ያበረከተ ሲሆን÷የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ መርሃ ግብርም ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው÷በሚዲያ ኢንዱስትሪው አንጋፋነቱን እያሳየ የሚገኘው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዛሬም እንደ ትናንቱ የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም የማህበራዊ አገልግሎቶችን እና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን ግንዛቤ በመፍጠር እና በማከናወን ሃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ፋና በሬዲዮ ፣ቴሌቪዥን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ መረጃን በማድረስ ፣ የማህብረተሰቡን ወግ፣ ባህል፣ እሴት እና መስተጋብር በማጉላት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማጋለጥ አበርክቶው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፋና ከዚህ ባሻገር የጀመራቸው የበጎ ፈቃድ ስራዎች እና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ÷ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መንግስት በበጎ ፈቃድ እና ችግኝ ተከላው ያደረገውን ጥሪ ተቀብሎ ከሙያዊ እገዛ ባለፈ በአካል ሊያግዝ በመገኘቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ከተማው ሰፊ የመሰረተ ልማት ችግር እንዳሉት ጠቁመው ፋና ይህን ተረድቶ ሊያግዘን በመምጣቱ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
በማርታ ጌታቸው

 

 

 

Exit mobile version