Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ደቡብ ኮሪያ በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርክ ጂን አስታወቁ፡፡

ፓርክ ጂን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ደቡብ ኮሪያ እና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት ወቅት ለደቡብ ኮሪያ ወታደሮችን በመላክ ያደረገችውን እገዛ የሀገሪቱ ሕዝቦች ምንጊዜም እንደማይረሱት አውስተዋል፡፡

ሀገራቱ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርም በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይም ሁሉን አቀፍ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በዚህ መሰረት በትምህርት፣ በጤና እና በግብርና ዘርፎች እንዲሁም በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ሀገራቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ለመፈራረም እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ በኢትዮጵያ በድርቅ እና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለችም ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍ ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

በንግድ ዘርፍ ያሉ እምቅ አማራጮችን መጠቀም እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ማጠናከር ላይ ሀገራቱ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኮሪያ ምሽት በሚል በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ 2030 ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትን ደቡብ ኮሪያ እንድታዘጋጅ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version