Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዕዙ በአማራ ክልል ሰላምን ለማረጋገጥ በቀጣይ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ላይ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነትን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በቀጣይ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ላይ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ።

ዕዙ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 13 ቀናት ያከናወናቸውን የተልዕኮ ተግባራት በጥልቅ በመገምገም ቀጣይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በሚመለከት አቅጣጫ አስቀምጧል።

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በግምገማው መሰረት በአማራ ክልል ሕዝቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን በሰራው ሥራ በአብዛኛው ሥፍራዎች ሠላምና ደኅንነት ተረጋግጧል ብሏል።

ለዚህ መሳካት ሰላም ወዳዱ የክልሉ ህዝብ የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደነበር በመግለፅ ምስጋናውን አቅርቧል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊና የጎንደር ቀጠና ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ደሳለኝ ጣሰው፣ በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አብዱ ሁሴን፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታና የማዕከላዊ ሸዋ ዞን ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አሕመዲን መሐመድ እንዲሁም በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊና የምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት አባል ይርጋ ሲሳይ እንደገለጹት፤ በክልሉ የዘራፊውንና ፅንፈኛውን ቡድን ምኞት በማክሸፍ ረገድ የክልሉ ህዝብ ሚና የላቀ ነበር።

በቀጣይም ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከክልሉ የፀጥታ ሃይሎችና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ሰላምን በዘላቂነት የማስተባበር፣ የተበታተነውን ፅንፈኛ ቡድን የማፅዳት እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በክልሉ የግልና የመንግስት ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የማድረግ ስራዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት።

በክልሉ የተገኘውን ሰላም የማጽናት ሥራ አጠናክሮ ለመቀጠል በተለይም ከኅብረተሰቡ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች አድማሳቸውን በማስፋት ከበርካታ የክልሉ ሕዝብ ጋር በመወያየት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ይሰራል ብለዋል።

የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች የሚታወቁና የክልሉ መንግስት የሚታገልላቸው መሆናቸውን በማንሳት፤ በቀጣይም ጥያቄዎቹ መልስ እንዲያገኙ በሰላማዊ መንገድ የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መንግስት የትኛውም ችግር በውይይት እንዲፈታ የማይናወጥ አቋም እንዳለው ገልጸው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም  ተግባር ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

Exit mobile version