Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ተቋርጦ የነበረው የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በካይሮ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ተቋርጦ የነበረው የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በዛሬው ዕለት በግብፅ ካይሮ ተጀምሯል።

የሶስትዮሽ ድርድሩ ከዚህ በፊት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ ሲደረግ ቆይቶ ረቂቅ ስምምነት ማዘጋጀት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ከዚያ ወዲህ ድርድሩ ሳይካሄድ መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከግብጽ ፕሬዚዳንት አብድል ፋታህ አል ሲሲ ጋር ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረጉት ምክክር÷ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፣ የውሃ አለቃቅ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ መምከራቸው ይታወሳል፡፡

በውይይታቸውም÷ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል የሚካሄደው የሦስትየሽ ድርድር እንዲቀጥል የደረሱትን መግባበት ተከትሎ ነው ዛሬ የሦስትዮሽ ውይይቱ የተጀመረው፡፡

የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርም÷ የሶስትዮሽ ድርድሩ በሶስቱ ሀገራት መካከል ትብብርን ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን የአሁንና የወደፊት ትውልድ ጥቅም ለማስጠበቅ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብት መሠረታዊ መሆኑንም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

ግድቡ ለሶስቱ ሀገራት የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ በፍትሀዊ እና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ አቋሟን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ድርድሩ በመግባባት እዲጠናቀቅም ኢትዮጵያ ትሠራለች ነው ያሉት፡፡

በረቂቅ ስምምነቱ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ድርድር እንደሚደረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

ድርድሩ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት እና የወደፊት የመልማት መብት ባስከበረ መልኩ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መከናወኑም ተገልጿል፡፡

Exit mobile version