አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ተቋማት ወጥ አሰራር እንዲኖራቸውና እርስ በርሳቸው እንዲናበቡ የሚያስችል ስርዓት ዛሬ ተመርቆ ወደ ስራ ገብቷል።
በስርዓቱ እስከ አሁን 20 የመንግስት ተቋማት አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ስርዓቱ የመልዕክት ልውውጥ፣ የቪዲዮ ኮንፈረንስ፣ የዴስክቶፕ ስታንዳርድ፣ የመረጃ ማጋራትንና ሌሎች አገልግሎቶችን እንደያዘ ተጠቁሟል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ÷የመንግስት ተቋማት ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ራሳቸው በቴክኖሎጂ የዘመኑ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የመንግስት ተቋማትን ዲጂታላይዝ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ ይህም ተቋማት ወረቀት አልባ አሰራር እንዲዘረጉ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
መረጃዎችና የመረጃ ልውውጡ በሚኒስቴሩ የመረጃ ማዕከል ስለሚተዳደር የመረጃ ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቅ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ስርዓቱ እስከ 20 ሺህ ሰዎችን ማስጠቀም የሚችል ሲሆን÷ በምስል፣ በድምፅ እና በጽሑፍ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ ያስችላል ተብሏል።