Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዱሱን አመት ስንቀበል ልምዶችን በመቀመር ለተጨማሪ ስኬት የሚያዘጋጁንን ሁኔታዎች በመጠቆም ይሆናል – መንግስት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዱሱን አመት ስንቀበል ለስኬት ያበቁንን ልምዶችና እሴቶች በመቀመር፣ ለተጨማሪ ስኬት የሚያዘጋጁንን ቀሪ ፈተናዎችን በድል ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በመጠቆም ይሆናል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ የአዲሱን አመት አቀባበል በተመለከተ በሰጡት መግለጫ እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት እንደ ሀገር የተመዘገቡ ስኬቶችን እና ፈተናዎች አንስተዋል፡፡

2015 ዓ.ም እንደ ሀገር ታሪካችንን የቀየሩ ድሎች የተመዘገቡበት አመት ነበር ብለዋል፡፡

ለአብነትም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ከውጭ የማስገባት ታሪክ ተቀይሮ ወደ ውጭ መላክ የተጀመረበት ዓመት መሆኑን አንስተው፤ ይህም እንደ ትልቅ ድል የሚነሳ ነው ብለዋል፡፡

በሚፈጠሩ እለታዊ ችግሮች እና ጩኸቶች ሳንንበረከክ ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን ከማረጋገጥ የሚያስቆም ሃይል እንደሌለ በስንዴ ምርት የተገኘው ተሞክሮ እና ልምድ የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የነበረው አውዳሚ ጦርነት በሰላማዊ ድርድር የተቋጨበት ዓመት መሆኑን አስታውሰው፤ የሰላም ስምምነቱም ኢትዮጵያን ከባሰ ጦርነት እና ከመበተን አደጋ ያዳነ ነው ብለዋል፡፡

በዲፕሎማሲው ዘርፍም ውጤት የተመዘገበበትና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ፣ በአሕጉራዊና በቀጠናዊ ደረጃ ተፅእኖ ፈጣሪና ተሰሚነቷ በእጅጉ ጨምሯል ያሉት፡፡

በዓመቱ ወሳኝ የሆኑ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ተከናውነዋል፤ ውጤትም ተገኝቶባቸዋል ብለዋል አቶ ከበደ፡፡

ጥበብ በተሞላበት የዲፕሎማሲ ስራ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆንም ችላለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም የዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ድል ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በ2015 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የተጠናቀቀበት ነበር፤ ይህም ለሀገራችን ክብር ያስገኘ ድል ነው ብለዋል፡፡

የተጠቀሱት በርካታ ድሎች ቢመዘገቡም የተለያዩ ተግዳሮቶችን አስተናግደናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኑሮ ውድነት፣ በየቦታው የነበሩ የሰላም መደፍረስ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት የ2015 ዓ.ም ፈተናዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

እነዚህን ለመቅረፍ በ2016ዓ.ም መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

አዲሱ አመትን ስንቀበል ድሎቻችንን በሚያፀኑ እና ፈተናዎችን በሚቀርፍ አኳኋን መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

እንዲሁም አዱሱን አመት ስንቀበል ለስኬት ያበቁንን ልምዶች እና እሴቶች በመቀመር ለተጨማሪ ስኬት የሚያዘጋጁንን ቀሪ ፈተናዎችን በድል ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በመጠቆም ይሆናል ብለዋል አቶ ከበደ፡፡

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version