አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት ቅድመ – ዝግጅት ያከናወናቸው ሥራዎችን አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
በዚሁ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ÷ የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት በቅድመ- ዝግጅት ሥራው በአቅም ግንባታ ሥራዎችና በአሰራር መመሪያዎች ማሻሻል ላይ ያለው አፈጻጸም አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም በሠራተኛ የሥራ አፈጻጸም ምዘናና በተቋሙ የውስጥ የመሰረተ-ልማት ግንባታ ማጠናቀቂያ ሥራዎች ላይ ያለው አፈፃፀም የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ምክር ቤቱን ማስተዋወቅ ሀገርን ማስተዋወቅ ነው ያሉት አፈ-ጉባዔው÷ በምክር ቤቱ የተጀመረው የሙዚዬም ግንባታና የቅርስ ማሰባሰብ ስራ በፍጥነት እንዲከናዎን አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
የምክር ቤቱ ም/አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው÷ ለምክር ቤቱ ሙያዊና አስተዳደራዊ ድጋፍ ለሚሠጡ የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች የተሠጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የምክር ቤት አባላትን አቅም በየፈርጁ ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት ከወዲሁ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡