Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮ-ሶማሊያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ጉባዔ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የኢትዮ-ሶማሊያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ጉባዔ በሞቃዲሾ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን÷የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ  ሕዝቦች በቋንቋ፣ ባህል እና ሌሎች እሴቶች  የተሳሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ለወንድማማች ሕዝቦች የሚጠቅሙ የትብብር መስኮችን ለማስፋት የሚያስችሉ እድሎችን የምንፈትሽበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ-ሶማሊያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ጉባዔ  በዋናነት በፖለቲካ እና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊያ ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ  መሆኑንም አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል፡፡

የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳላህ አህመድ ጃማ በበኩላቸው÷የኢትዮ-ሶማሊያ  የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ጉባዔ የሀገራቱን ሕዝቦች የሚጠቅም ታሪካዊ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ጉባዔው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ትሰራለች ብለዋል፡፡

ከኢትዮ-ሶማሊያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ በሀገራቱ መካከል የንግድ ትብብር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version