Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቦርዱ በህግ ጥላ ሥር ስላሉ ተጠርጣሪዎች ሁኔታ ምልከታና ምርመራ ማድረጉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በህግ ጥላ ሥር ስላሉ ተጠርጣሪዎች (እስረኞች) ሁኔታ ምልከታና ምርመራ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ምልከታና ምርመራ ባደረገበት ወቅት ያያቸውን ጠቅላላ ሁኔታዎች ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም÷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በክልሉ በተቋቋሙት አራት ኮማንድ ፖስቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ማዕከላት ላይ በተለያዩ ጊዜያት በአካል በመንቀሳቀስ በህግ ጥላ ሥር ስላሉ ተጠርጣሪዎች (እስረኞች) ሁኔታ ምልከታና ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ቦርዱ በመግለጫው እንዳስታወቀው÷ በባህር ዳር፣ ኮምቦልቻ፣ ሸዋ ሮቢት እና ጎንደር ከተማ ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ላይ የመስክ ምልከታ አከናውኗል፡፡

በዚህም በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችና የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ ያደራጃቸው ኮማንድ ፖስቶች እንዲሁም የጊዜያዊ ማቆያ አስተባባሪዎች ወይም የማረሚያ ቤት አስተዳደር አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

እንዲሁም በህግ ጥላ ሥር ያሉ ተጠርጣሪዎች (እስረኞች) ከተያዙበት ቀን ጀምሮ ያለው ሰብአዊ አያያዝ ሁኔታ ጥሩ መሆኑን ቦርዱ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

ቦርዱ ከተጠርጣሪዎች ጋር በነበረው ውይይት የተነሱ ዋና ዋና ጭብጦች መያዙን ጠቁሞ፤ ከአቆያየት ጋር በተያያዘ በተጠርጣሪዎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ አያያዞች አለመኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል ቦርዱ፡፡

በህግ ጥላ ሥር ለሚገኙ ተጠርጣሪዎች መቅረብ ያለባቸው መሰረታዊ አገልግሎቶች እየቀረቡ መሆናቸውን (ምግብ፣ መኝታ መፀዳጃ፣ ህክምና፣ ወዘተ) ማረጋገጡን ገልጿል።

በህግ ጥላ ሥር ለሚገኙ ተጠርጣሪዎች በቤተሰብ እንዲጎበኙ የማድረግ ሁኔታው በአንዳንድ ማእከላት ውስንነት እንዳለ ማረጋገጡን ጠቅሷል፡፡

የተጠርጣሪዎችን ሁኔታ ለመለየት እና ቀጣይ የሚኖረውን አካሄድ ለመወሰን የፖሊስ ምርመራዎች በተለያየ ደረጃ ያሉ መሆኑን ገልፆ÷ የፖሊስ ምርመራዎች በከፊል የተጀመሩባቸው እንዲሁም ምርመራዎች ተጠናክረው የቀጠለባቸው ማእከላት መኖራቸውን ለማየት ተችሏል ብሏ፡፡

የታሰሩ ግለሰቦች ስም ዝርዝር ማወቅና መያዝ መቻሉን ጠቁሞ÷ በአምስቱ ማእከላት ብቻ 764 ተጠርጣሪዎች በህግ ጥላ ሥር የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ነው ያለው፡፡

የታሰሩ ሰዎች ማቆያ ቦታ ለውጥ በተመለከተ÷ ወንድ ተጠርጣሪዎች ከአዲስ አበባ ወንጀል ምርመራ ወደ አዋሽ አርባ መዘዋወራቸውን ገልጾ÷ ውስን ቁጥር ያላቸው ሴቶች በአዲስ አበባ በነበሩበት ወንጀል ምርመራ ማዕከል እንዲቆዩ ተደርጓል ብሏል፡፡

የፖሊስ ምርመራ ባለሙያዎችን ቁጥር በመጨመር፣ የወንጀል ምርመራውን በማፋጠን፣ የምርመራ ውጤቱን መሰረት በማድረግ ተገቢነት ያላቸውን የህግ አማራጮች በመጠቀም በቂ ማስረጃ የማይገኝባቸውን እንዲለቀቁ ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል፡፡

እንዲሁም ተጨማሪ ምርምራ የሚያስፈልግባቸውን እንደሁኔታው በቂ ዋስትና በማስቀረብ የሚፈቱበትን ሁኔታ መፍጠር ወጣት ጥፋተኞችን በመለየት በህጉ በተቀመጠው አማራጭ የምክር እና ጸባይ ማረሚያ አማራጮችን መተግበር በወንጀል ውስጥ መሳተፋቸው በቂ ማስረጃ ያለባቸውን ተጠርጣሪዎችን ቶሎ ክስ መመስረት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ለሴት ተጠርጣሪዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ምርመራው በልዩ ሁኔታ በአጭር ጊዜ የሚከናወንበትን ሁኔታ እንዲፈጠር አሳስቧል፡፡

ቦርዱ በቀጣይ የተሰጡ ምክረ-ሀሳቦች ስራ ላይ መዋላቸውና መሻሻሎች መታየታቸውን ማረጋገጥ፣ ጥቆማ የቀረበባቸውን እና የመስክ ምልከታ ያልደረሰባቸው ተጠርጣሪ ማቆያ ቦታዎችን መጎብኘት/መፈተሽ እንደሚያከናውን ገልጿል፡፡

Exit mobile version