አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቻይና ጂያንግሱ ግዛት ሊያንዩንጋንግ ከተማ “አንድ ዓለም፤ የጋራ ደኅንነት” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የሕዝብ ደኅንነት ትብብር ፎረም ላይ ተሳተፈች፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት እና የዓለም አቀፍ የሕዝብ ደኅንነት ትብብር ፎረም ቦርድ አባል÷ በኢትዮጵያ ያለውን የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የሪፎርም ሥራዎችና የተገኙ ስኬቶችን በፎረሙ ላይ አቅርበዋል፡፡
ከፎረሙ ጎን ለጎን ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ፕሬዚዳንት፣ ከቻይናው የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዋንግ ዥያሆንግ እና ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሜጀር ጀኔራል አሕመድ ናስር አል-ራይሲ ጋር መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም በሀገራቱ እና ከኢንተር ፖል ጋር የተጀመሩ ትብብሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
የኢንተርፖል ፕሬዚዳንት በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉም ተጠቁሟል፡፡