አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮሌራ ከተከሰተባቸው 229 ወረዳዎች አሁን ላይ ወረርሽኙን በ110 ወረዳዎች መቆጣጠር መቻሉ ተመላከተ፡፡
በወቅታዊ የድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ላይ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም÷ በአማራ ክልል በተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ የድንገተኛ ምላሽ አሳጣጥ የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት እና በመንገድ ችግር አቅርቦትን ማድረስ አለመቻሉ እንደተግዳሮት ተነስቷል፡፡
ይሁን እንጂ በጤና ሚኒስቴር በኩል በአራት ዙር ለክልሉ መድሃኒት እና ቁሳቁስ በአውሮፕላን ቀርቧል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በ10 ክልሎች ኮሌራ ከተከሰተባቸው 229 ወረዳዎች አሁን ላይ በ110 ወረዳዎች የነበረውን ወረርሽኝ መቆጣጠር ተችሏል መባሉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የኩፍኝ ወረርሽኝን 94 በመቶ መቆጣጠር ቢቻልም አሁንም በ17 ወረዳዎች ላይ ወረርሽኙ መኖሩ ተጠቁሟል፡፡
የወባ ወረርሽኝ በሁሉም ክልሎች መከሰቱ እና በተወሰኑ አካባቢዎች የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ ስለመሆኑም በውይይቱ ቀርቧል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የወባ መከላከያ ቁሳቁስ ስርጭት መስተጓጎሉም ነው የተገለጸው፡፡
አጋር ድርጅቶች የመድኃኒትና ሕክምና ግብዓት ድጋፍ እንዲያደርጉ እና የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም ግብዓቶቹን በማድረስ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጠይቀዋል፡፡
ወረርሽኞች በተደጋጋሚ የሚከሰቱበትን ምክንያት ማወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ አጋር ድርጅቶች ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች እንዲገቡና ድጋፍ አሰጣጡ ከመንግስት የጤና ሥርዓት ጋር በቅንጅት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም የጸጥታ ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው÷ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
በተለያየ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠትና መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላትም የአጋሮች ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡